‎በብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ እመርታዊ ለውጥ በማምጣት የማህበረሰቡን ህይወት በተጨባጭ ሊቀይር በሚችል መልኩ በቁርጠኝነት መስራት ይገባል፦ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)

በመደመር መንግሥት ዕይታ የዘርፎች እመርታ “በሚል ሀሳብ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ ዙር የከፍተኛና መካከለኛ አመራር ስልጠና ለቀጣይ ተልዕኮ ዝግጁነት በመፍጠር በስኬት ተጠናቋል። ‎ ‎በስልጠናው ማጠቃለያ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) እንዳሉት እንደ ሀገር በብዝሃ ዘርፍ ላይ እመርታዊ ለውጥ በማስመዝግብ የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል። ‎ ‎እስካሁን የተገኙ ውጤቶችን አስጠብቆ በማስፋት በመደመር መንግስት እይታ በብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ እመርታዊ ለውጥ በማምጣት የማህበረሰቡን ህይወት በተጨባጭ ሊቀይር በሚችል መልኩ መስራት ይገባል ብለዋል። ‎ ‎አመራሩ ችግሮችን ለመሻገርና ዐቅሞቻችንን በአግባቡ ለመጠቀም አዳዲስ ምልከታዎችና ከፍ ባለ ምናብ በፈጠራ ፣በፍጥነትና ዝላይ እሳቤዎችን በቁርጠኝነት በመተግበር እመርታዊ ለውጥ ለማምጣት ትኩረት የሚሻው ጉዳይ እንደሆነ አሳስበዋል። ‎ ‎የግብርና ምርታማነትን ለማሻሻል በሚረዱ አሠራሮች ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ‎ኩታ ገጠም እርሻ፣ ያልለሙ መሬቶችን ማልማት ፣የምርጥ ዘርና ማዳበሪያ አጠቃቀም ማሳደግና ሜካናይዜሽን እርሻን በመጠቀም የቤተሰብ ብልጽግናን እና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት መስራት ይጠበቃል ብለዋል። ‎ ‎የግብርና ትራንስፎርሜሽን ውጤታማ ለማድረግ በአግሮፕሮሰሲንግ ፣በኮመርሻላይዜሽንና እሴት የሚጨምሩ አሰራሮቹን መተግበር ያስፈልጋል ያሉት ርዕሰመስተዳድሩ የገጠር ፣የኢንዱስትሪያላይዜሽንና የከተማ ሽግግርን ውጤታማ ማድረግ ዋነኛ ተግባር እንደሆነ አስገንዝበዋል። ‎ ‎በሌማት ትሩፋት ፣በአረንጓዴ አሻራ በከተማና በገጠር ኮሪደር፣በመሶብ አገልግሎት እንዲሁም በፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት በቅንጂታዊ አንድነት አሰራሮችን በማሳለጥ ተጨበጭ ለውጥ ለማስመዝገብ በጊዜ የለንም መንፈስ መስራት ይገባል ብለዋል። ‎ የጊዜ አጠቃቀምን በመግራት ከተለምዷዊ የሥራ ባህል ባሻገር ያመለጡንን ዕድሎች በቁጭት ለማካካስ በሚያስችል ደረጃ በመንቀሳቀስ ብልጽግናን ማረጋገጥ ተቀዳሚ ተግባር መሆን እንዳለበት አንስተዋል። ‎ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ዘላቂነት ያለው አስተማማኝ ኢኮኖሚ ለመገንባት የበረታን ሁነን መገኘትን ጊዜው ይጠይቃል ነው ያሉት። ‎ ‎አመራሮች በንድፈ ሀሳብ የወሰደቱት ስልጠና ተግባራዊ በማድረግ የህዝቡን ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን አጠናክረው እንዲወጡ አስገንዝበዋል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *