ABOUT US
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አጠቃላይ ገጽታ
በቀድሞ የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ስር የነበሩ የካፋ፣ የዳውሮ፣ የቤንች ሸኮ፣ የሸካና የምዕራብ ኦሞ ዞኖች እና የኮንታ ልዩ ወረዳ ህዝቦች የዘመናት በክልል የመደራጀት ጥያቄ የብልፅግና ፓርቲ በሚመራው የለውጡ መንግስት ምላሽ በማግኘቱ በህዳር 14/2014 ዓ.ም የፌደሬሽኑ 11ኛ ክልል ሆኖ የተመሠረተ ክልል ነው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፡፡
ክልሉ የኮንታ ልዩ ወረዳ ህዝቦችን በዞን የመጀራጀት የዘመናት ጥያቄ ወዲያውኑ በመመለስ ስድስት ዞኖችን አቅፎ የተደራጀ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት 20 የከተማ አስተዳደሮች፣ 41 የወረዳ አስተዳደሮች፣ 806 የገጠር ቀበሌ አስተዳደሮችና 100 የከተማ ቀበሌ አስተዳደሮች (በድምሩ 906 ቀበሌዎች) ያሉት ነው፡፡
የክልሉ አጠቃላይ የቆዳ ስፋቱ 39,061.4 ስኩዌር ኪሎሜትር (3.91 ሚሊዮን ሄክታር) እንደሚሆን ይገመታል። ክልሉ በሰሜን አቅጣጫ ከኦሮሚያ ክልል፣ በምዕራብ በኩል ከጋምቤላ ክልል፣ በስተደቡብ እና በስተምስራቅ በኩል ከደቡብ ሱዳንና ኬንያ ሀገራት፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልና ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ጋር ይዋሰናል።
ክልሉ የብዝሃ-ማዕከላት አደረጃጀትን ለሀገሪቱ ያስተዋወቀ ሲሆን አራት ዋና ከተሞችና ሁለት ተደራሽ ከተሞች ያሉት ሲሆን እነሱም፣ ቦንጋ የክልሉ የፖለቲካና አስተዳደር መቀመጫ፣ ታርጫ የክልሉ ህግ አውጪ (ምክር ቤት) መቀመጫ፣ ሚዛን-አማን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ መቀመጫና ቴፒ የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት መቀመጫ ሲሆኑ አመያና ጀሙ ከተሞች ደግሞ የተወሰኑ የክልሉ ባለስልጣን መስሪያቤቶችና ኤጀንሲዎች መቀመጫ ናቸው፡፡
በአራቱ ዋና ከተሞች የክልሉ አስፈጻሚ ቢሮዎችና ሌሎች መስሪያቤቶች የተከፋፈሉ ሲሆን ይህም ፍትሀዊ የከተሞች ልማት እንዲኖር ከማድረጉ ባለፈ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ህብረ-ብሔራዊ አንድነት እንዲሰፍን የጎላ ሚና ይጫወታል፡፡
የ1999 ዓ.ም የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ውጤትን መሠረት በማድረግ በተደረገው ትንበያ በ2016 የበጀት ዓመት የክልሉ ህዝብ ብዛት 3,837,201 እንደሆነ የሚገመት ሲሆን ከአጠቃላይ የህዝብ ብዛት በገጠር 84.73% እና በከተማ 15.27% ይኖራል።
በክልሉ በስድስቱ ዞኖች 13 ነባር ብሔር፣ ብሔረሰቦች በህገ መንግስታችንም ላይ የህዝቦች ክልል ተብሎ አንደተጠቀሰው ከሌሎች ከተለያዩ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር ተባብረው፣ ተዛምደውና ተጋምደው በሠላም፣ በመከባበርና በመቻቻል ይኖራሉ። እነሱም ካፈቾ፣ ናኦ፣ ጫራ፤ ሸካቾ፣ ሸኮ፣ ማጃንግ፣ ቤንች፣ ሜኤኒት፣ ሱሪ፣ ዲዚ፣ ዝልማሞ፣ ዳውሮ እና ኮንታ ብሔር-ብሔረሰቦች ናቸው። አብዛኛው የክልሉ ህዝብ ኑሮ የተመሰረተው በግብርና ላይ ሲሆን አርብቶ አደሮችም በክልሉ በካፋ እና በምዕራብ ኦሞ ዞኖች ውስጥ ይገኛሉ፡፡
በሀገሪቱ ከሚገኙ ብሔራዊ ፓርኮች ውስጥ የኦሞ እና ጨበራ ጬርጬራ ብሔራዊ ፓርኮች የሚገኙበት ክልል ሲሆን በተጨማሪም በካፋና በሸካ ዞኖች በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ፣ የትምህርትና የባህል ድርጅት (UNESCO) የተመዘገቡ ለቱሪዝም ልማት ዕምቅ አቅም ያላቸው ሁለት ባዮስፌር ሪዘርቮች ይገኛሉ።
ከእነዚህና ከመሳሰሉት የደን ሀብቶች የሚገኘውና በጥራቱ ተወዳዳሪ የሌለው የጫካ ማርም ሌላው የክልሉ መገለጫ ነው፡፡ በቀጣይ ተከልለው በፓርክነት ለምተው ለቱሪዝም ልማት ሊውሉ የሚችሉ ትላልቅ ፏፏቴዎች፣ ፍል ውሃዎች፣ የተፈጥሮ ድልድዮችና የመሳሰሉት ስፍራዎች በክልሉ ይገኛሉ።
ክልሉ በርካታ የገፀ-ምድር ውሀ ሀብት ባለቤት ሲሆን ለተለያዩ የኤልክትሪክ ኃይል ማመንጫና መስኖ ልማት ግድቦች አመቺ የሆኑ እንደ ኦሞ፣ ኪቢሽ፣ ካሹ፣ ጎጀብ፣ ባሮ፣ ሻርማ፣ ቢቲኖ፣ ዲንቻ፣ ባቆ፣ ጋቸብ፣ ኮቶሮ፣ ዞአ፣ ማንታ፣ ማናሾ፣ ጋሀማዎ እና የመሳሰሉ ትላልቅ ወንዞች ይገኙበታል፡፡
ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቀጥሎ ትልቁ ለሀገርቱ የኤልክትሪክ ኃይል አቅራቢ የግቤ ሶስትና አራት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች የሚገኙት በዚህ ክልል ነው፡፡ በዳውሮ ንጉስ ሐላላ የተገነቡ ረጃጅም የድንጋይ ግንቦች ዙሪያውን ያጠሩ የሀላላ ኬላ እና በአለም ረጅሙ የትንፋሽ የሙዚቃ መሳሪያ (ዲንኬ) በክልሉ ከሚገኙ የቱሪዝም ሀብቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ።
በክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ሀሳብ አመንጪነት በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የተገነቡ ሀላላ ኬላ ሪዞርትና የዝሆን ዳና ሎጅ እንዲሁም በደንቢ ሰው ሰራሽ ሀይቅ አከባቢ እየተገነቡ ያሉ የገበታ ለትውልድ አካል የሆነው ሎጅ፣ የሚዛን-አማን አለምዓቀፍ እና የቦንጋ መለስተኛ አውሮፕላን ማረፊያዎች በክልሉ ከሚገኙ የቱሪስት ሳቢ ልማቶች ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ክልሉ በማዕድን ሀብቱም የታወቀ ሲሆን ለአብነት ሊጠቀሱ የሚችሉ የኢንዱስትሪ፣ የኮንስትራክሽንና የከበሩ ማዕድናት ይገኙበታል፡፡ ለአብነትም ወርቅ፣ ብረት፣ የድንጋይ ከሰልና ሌሎችም በክልሉ ውስጥ በስፋት ይገኛሉ፡፡ በተለይ የምዕራብ ኦሞ ዞን ውስጥ የሚገኙ የቤሮና ሱርማ ወረዳዎች ከፍተኛ የወርቅ ክምችት ያላቸው ከመሆኑም በላይ በሀገሪቱ ከሚጠቀሱ ወርቅ አምራች ቀጠናዎች ውስጥ ይመደባሉ፡፡
ክልሉ በሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው የተለያዩ እምቅ የተፈጥሮና የግብርና ሀብቶች ባለቤትም ነው፡፡
አብዛኛው የክልሉ አካባቢዎችም የቡና አምራች ናቸው፡፡ በመሆኑም ከኦሮሚያ ክልል ቀጥሎ በሀገሪቱ ከፍተኛ የቡና አምራችና ለገበያ አቅራቢ ክልል ነው፡፡ የሀገሪቱን ከፍተኛ የሻይ ምርት ለሀገር ውስጥና ለውጪ ገበያዎች የሚያቀርቡ የውሽውሽና የጫዋቃ ሻይ ልማቶችም በክልሉ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም የተለያዩ የቅመማቅመም ምርቶች እንደ ኮረሪማ፣ ጥሚዝ፣ ዝንጅብል፣ ቁንዶበርበሬ፣ እርድ እና የመሳሰሉት በክልሉ በስፋት ይመረታሉ፡፡ ፍራፍሬም እንደ ሙዝ፣ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ አናናስ ያሉ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የሚመረቱ ሲሆን በሀገሪቱ ገበያም ከፍተኛ ድርሻ አላቸው፡፡
ከዚህም በላይ ቀላል የማይባል የእንስሳት ሀብት በክልሉ ይገኛል፡፡ የቀንድ ከብቶች፣ በጎችና ፍየሎች በስፋት ይረባሉ፡፡ በሀገሪቱ በግዝፈቱና በስጋ ጥራቱ የሚታወቅ የቦንጋ በግ እንዲሁም ገንዲ በሽታን በመቋቋምና ከፍተኛ የወተት ምርት በመስጠት የሚትታወቅ የሸኮ ጎዳ ላም ዝሪያም ሌላኛው የክልሉ ገፀ-በረከቶች ናቸው
የደቡብ ምዕራብ ክልል መንግስት ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት በስሩ 6 የዞን 40 የወረዳ እና 20 የከተማ አሰተዳደር መዋቅሮች ያሉት ሲሆን
- 2927 የፓርቲ ህብረት
- 16731 የቤተሰብ አደረጃጀት
- እና በስሩ 544535 አባላት ይፐኛሉ


