የፓርቲና የመንግስት ግቦችን ለማሳካት አመራሩ በቁርጠኝነት መስራት አለበት፦አቶ በላይ ተሰማ

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የድጋፍና ክትትል ሱፐርቪዥን ቡድን በሸካ ዞን በሚያካሂዳቸው የፓርቲና የመንግስት ሥራዎች የድጋፍና ሱፐርቪዥን ዙሪያ ከሸካ ዞን ከፍተኛ አመራሮች ጋር በቴፒ ከተማ ውይይት አካሂዷል።

የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ በላይ ተሰማ በፓርቲ እና በመንግስት የተቀመጡ ግቦችን ከዳር ለማድረስና ውጤታማነትን በላቀ ደረጃ ለማረጋገጥ ድጋፋዊ የሱፐርቪዥን ስራዎች ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

የፓርቲና የመንግስት ስራዎችን በተቀናጀና በተናበበ መልኩ አመራሩ ተግባራትን በቁርጠኝነት መፈጸምና ማስፈጸም ይገባል ያሉት አቶ በላይ እስካሁን የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማስቀጠልና ጉድለቶችን ለይቶ ለቀጣይ ተግባራት ስኬት መፍትሔ ማበጀት የምልከታው ዓላማ እንደሆነ አመላክተዋል።

የህዝቡን ተጠቃሚነት ሊያረጋግጡ የሚያስችሉ በፓርቲያችን የተጀመሩት ኢኒሼቲቦችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችል አስቻይ ሁኔታዎችን በመለየት የክልሉ ድጋፍና ክትትል ቡድን በዘላቂነት እስከ ጥር 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የድጋፍና ክትትል ሥራዎችን በዞኑ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

የብልጽግና ቤተሰብና የብልጽግና ህብረት በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ትኩረት አድርጎ ውይይት ማድረግ እና ድሎችን በማስቀጠል መሻሻል ያለባቸውን በፍጥነት የማረም ሥራ መሰራት ይገባል ብለዋል።

የሸካ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አለማየሁ አለሙ በበኩላቸው በዞኑ የተጀመረውን ሁለንተናዊ ብልፅግናን የማረጋገጥ ሥራዎችን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የፓርቲና የመንግስት ስራዎችን በላቀ ዝግጁነት በመፈጸም ይሰራል ብለዋል።

ድጋፋዊ ሱፐርቪዥኑ ሚናው ስኬት ከመቀመርና ጉድለቶችን ከመማር ባሻገር የተሻሉ አቅሞችን ወደ ታች ለማውረድ የሚያስችል መሆኑን በመግለጽ የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በፓርቲያችን የተጀመሩት ኢኒሼቲቦችን እና የንቅናቄ አጀንዳዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ነው ያሉት አቶ አለማየሁ።

በሸካ ዞን እስካሁን የተከናወኑ የፓርቲ እና የመንግስት ስራዎች አፈፃፀምን በሚመለከት ለድጋፍና ክትትል ቡድኑ የሸካ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት የፖለቲካና ህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዘርሁን አንደሞ አቅርበዋል።

በዞኑ ባሉት ወረዳዎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና በቀበሌዎች ደረጃ የድጋፍና ክትትል ስራዎች እንደሚሰሩ ተመላክቷል።

በመድረኩ የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ በላይ ተሰማን ጨምሮ የድጋፍና ክትትል ቡድን፣የዞኑ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት እና የሴክተር መስሪያ ቤት አስፈፃሚ አካላት ተገኝተዋል ሲል የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *