የክልሉ መንግሥት ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመቀናጀት ለሁለንተናዊ ለውጥ ይሰራል:- አቶ ፍቅሬ አማን

በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሠላማዊ የመማር፣ ማስተማር ስራ እንዲቀጥል በማድረግ ብቁ ዜጋን ለማፍራት ያለመ ከክልሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አመራሮችና የባለድርሻ አካላት በቦንጋ ከተማ የውይይት መድረክ እያካሄደ ይገኛል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን በውይይቱ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት በክልሉ እስካሁኑ ጉዞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አስተዋጽኦ የጎላ እንደነበርና ይህንን ግንኙነት አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት ይሰራል።

ዩኒቨርስቲዎች የእውቀትና ክህሎት ማዕከል መኾኑን የጠቆሙት አቶ ፍቅሬ ይህንን መልካም ዕሴት በሀገር ግንባታ ላይ በተገቢው እንዲወጡ በጠንካራ መሠረት ላይ የተጣለ ግኑኝነት መፈጠር አለበት ብለዋል።

በመኾኑም፥ የክልሉ መንግሥት በክልሉ እና ከክልሉ ውጪ ከሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመቀናጀት በዘርፍ ብዙ ተግባራት ላይ በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መኾኑንም አቶ ፍቅሬ ተናግረዋል።

የክልሉን የልማት ፀጋዎች ወደ ሚጨበጥ ሀብትነት በመቀየር የኅብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ በሚደረገው የመንግሥት ጥረት ዩኒቨርሲቲዎች በጥናትና ምርምር ስራዎቻቸው መደገፍ እንደሚገባም ነው አቶ ፍቅሬ ያስገነዘቡት።

በዩኒቨርስቲዎች ሠላማዊ የመማር ማስተማር ስራ እንዲቀጥል ከአደረጃጀቶች ጋር በቅንጅት ከሚሰሩ ተግባራት በተጨማሪ የውስጥ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታትና የአግልግሎት አሰጣጥ ማሻሻልን ትኩረት አድርገው መስራት አስፈላጊ መኾኑንም አቶ ፍቅሬ ተናግረዋል።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ነጻና ገለልተኛ ኾነው የመማር ማስተማር ተግባር እንዲቀጥል የባለድርሻ አካላት ቅንጅት መጠናከር እንዳለበት ያስገነዘቡት የክልሉ ረዳት የመንግሥት ተጠሪ አቶ ነጋ አበራ፥ ግኑኝነትን በማሻሻል በጋራ፣ በትብብር መንፈስ መስራት ይገባል ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *