አመራሩ የአገልጋይነት እሳቤን በመላበስ የድህረ ምርጫ ግቦችን በላቀ ትጋትና ቁርጠኝነት መፈጸም አለበት ፦አቶ ፍቅሬ አማን
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ስራ አመራር ኮሚቴ በድህረ ምርጫ ግቦች አፈጻጸም ላይ ያተኮረ ግምገማ በማካሄድ የቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።
በግምገማ መድረኩ ላይ በድህረ ምርጫ ወቅት የታቀዱ ሥራዎችን በውጤታማነት በመፈፀም ቅቡልነት ያለው ጠንካራ መንግስት የመመሥረት ግብን በተሟላ ሁኔታ ለማሳካት ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ተመላክቷል።
በመድረኩ በክልሉ በብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን አመራሩና አባሉ በድህረ ምርጫ ወቅት የተጀመሩ ሥራዎች ግለታቸውን ጠብቀው እንዲቀጥሉ የመፈጸምና የማስፈጸም ኃላፊነት መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
መደበኛ የፖለቲካ ሥራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ከፍ ማድረግ የአመራሩ ቀዳሚ ኃላፊነት እንደሆነም ገልጸዋል።
አመራሩ የሕዝብ አገልጋይ እሳቤዎችን በመላበስ በላቀ ትጋትና ቁርጠኝነት ወደ ተግባር መግባት እንዳለበት የገለጹት አቶ ፍቅሬ የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን እንዲሁም የመንግስትን የአገልግሎት አሰጣጥ በላቀ ትጋትና ፍጥነት በውጤታማነት እንዲፈጽም የመሪነት ሚና መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።
የህዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጡ የሚያስችሉ በፓርቲ መሪነት የሚፈጸሙ ታላላቅ የልማት ኢኒሼቲቦች ግለታቸውን ጠብቀው እንዲቀጥሉ ማስቻል ይጠበቃል ነው ያሉት።
በየደረጃው ያለው አመራርና አባላት የሕዝብን አመኔታ በሚያፀና መልኩ ኃላፊነቱን በብቃት እንዲወጣ አሳስበው የቀጣይ ጊዜያት ትኩረት አቅጣጫ አስቀምጠዋል።


