ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በቦንጋ ከተማ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ።


ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በቦንጋ ከተማ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በቦንጋ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል።

የክልሉን ሁለንተናዊ ገጽታ የሚቀይሩና የሕዝቡን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ቀንና ሌሊት በተፋጠነ ፍጥነት እየተገነቡ እንደሚገኝ በጉብኝቱ ወቅት ተገልጿል።

ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በቦንጋ ከተማና በአካባቢው እየተከናወኑ ያሉ ወሳኝ የልማት ሥራዎችን በአካል ተገኝተው የጎበኙ ሲሆን፣ ፕሮጀክቶቹ በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ተጠናቀው ለሕዝብ አገልግሎት እንዲበቁ አሳስበዋል።

በዚህም ግንባታው እየተፋጠነ የሚገኘውና የመሬት ሥራው አልቆ 20 ከመቶ የፊዚካል ሥራው የተጠናቀቀው ግዙፉ የክልል ተቋማት ሕንጻ፣ እንዲሁም በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አማካኝነት ግንባታው እየተከናወነ ያለውን የቦንጋ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ያለበት ደረጃ ላይ ምልከታ ተደርጓል።

በዚህም የ1.8 ኪሎሜትር የአውሮፕላን መንደርደሪያ የአፈር ቆረጣ ሥራው ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ የአፈር ሙሌትና መሠረት የማንጠፍ ሥራው እየተገባደደ የሚገኝ ተመላክቷል።

በክልሉ መንግሥት የበጀት ድጋፍ በጊንቦ ወረዳ ሾምባ ከጪብ ቀበሌ እየተገነባ የሚገኘውና ግንባታው ሊጠናቀቅ የተቃረበው የገጠር ሞዴል መንደርም ሌላኛው የጉብኝቱ አካል ነበር።

ይህ በጊንቦ ወረዳ በልዩ ትኩረት እየተገነባ የሚገኘው የገጠር ሞዴል መንደር፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የገጠር ኮሪደር ልማት ኢንሼቲቭ አካል ተደርጎ በክልሉ መንግሥት እየተገነባ ነው።

በመሆኑም በክልሉ እየተገነባ ያለው ይኸው ሞዴል መንደር የገጠሩን ማኅበረሰብ የኑሮ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ በማሻሻል፣ መሠረተ ልማትን በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ ለማስፋፋት እንዲሁም የገጠር ከተሞችን የሥራ ዕድልና የኢኮኖሚ ማዕከል ለማድረግ የታለመ መኾኑ በጉብኝቱ ወቅት ተገልጿል።

በጉብኝቱ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ማስረሻ በላቸውን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት የሥራ ሀላፊዎች ተሳትፈዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *